ትውስታ

ታላቁ ባለቅኔና የተውኔት አዘጋጅ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ዘመን ተሻጋሪ የሆነችውን “ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” የምትለዋን ግጥም የፃፈው፡ አንድ ቀን ምሽት ከማዘጋጃ ቤት ሲወጣ ባየው ትዕይንት ምክንያት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡ ፀጋዬ ገ/መድህን ከማዘጋጃ ቤት እንደወጣ ቁልቁል ወደ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሲያመራ አንድ ጀብራሬ (በሎሬቱ አነጋገር) ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ላይ ሸንቱን ሲሸና ተመለከተ፡፡ ፀጋዬም በደም ፍላት ወደ ጀብራሬው ተንደረደረ፡፡ ጀብራሬው ግን “አንተ ድንጋይ እሸናብሃለሁ፡፡ ድንጋይ ነህ …. ድንጋይ ነህ ….” እያለ በሐውልቱ ላይ ይሸናል፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር ሎሬቱ “ጴጥሮስ ድንጋይ አይደለም” ብሎ ጀብራሬውን በደም ፍላት ዘሎ ያነቀው፡፡ ከዚያም አብረውት የነበሩት ሰዎች ገላገሉትና እየተብሰከሰከ አራት ኪሎን ተሻግሮ ቀበና ገባ፡፡ማታውን አልተኛም፡ አነሆ “ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” የምትለዋን ግጥምና ኑዛዜ ሲጭር አደረ፡፡ምንጭ፧ የፌስቡክ ገጽ #ADWA

@@@@@@@@@@@@@@@@@@@@
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ ጀግኖች

አዬ! ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?ልቦናሽን ታዞሪባት?ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?አላንቺ እኮ ማንም የላት….አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣እንደኮረብታ ተጭኗት ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝእመ ብርሃንቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ እሸሸግበት ጥግ አጣሁ እምፀናበት ልብ አጣሁ እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ ….አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ ከእናቴ ማኅፀን አርፌ ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ ከወዟ ወዜን ቀፍፌ በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤ በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደ ወንዙ ፍሳሽ በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ ለግልገሌ ካውሬ ከለል እማሳው ሥር ጎጆ መትከል ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል። ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት እመ ብርሃን እረሳሻት? ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት ያቺን የልጅነት እናት? አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት? ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ባገልግሎትሽ ስዋትት ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፣ ከድጓ ቤት እመጻሕፍት ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፣ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ ከቀፈፋ ደጀሰላም፣ ከቤተልሔም ቅዳሴ እኰ፣ ቀፎ ዳባ ለብሶቅኔ ዘርፎ ግስ ገሦ መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ በልብስ ተክህኖ አጊጦ፣ በብር አክሊል ተሸልሞ እመ ብርሃን ያንች ጽላት፣ ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ የመናኒው ያባ ተድላ፣ ረድ ሆኜ፣ አብሮኝ ታድሞ ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ.ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፣ከምትሰጪኝ የፍርሃት ጦስ ምነው በረኝነት እድሜ፣ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፣ ወርዶ በጨለማ በርኖስ። ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ከነደደችበት እቶን የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡ …..አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ እምፀናበት ልብ አጣሁ፡፡.ሕፃን ሆኘ የእርግብ ጫጩት አንዳንዴ ርሃብ ሲያዳክማት ችጋር ከጎጆዋ ገፍቶ እዛፍ ግርጌ ሲጥላት እናቷ በርራ ደርሳላት በአክናፏ ሙቀት ተታቅፋት እፍ እያለች ግንባሯ ላይ ህይወት ስትተነፍስባት ወዲያው ነፍስ ትዘራለች ሽር-ብር-ትር እያለች ። ባክሽ አንችም አትራቂብኝ እመብርሃን እናቴ ትንፋሽሽን እፍ በይብኝ ፅናትሽን እፍ በይብኝ ፤ወይም ይችን የሞት ጽዋ ፥ጥላዋ ነፍሴን ካፈናት እንዳልጠጣት አሳልፊያት መራራ ክንፏን ገንጥለሽ ቀጠሮ ቃሏን ግደፊያት። አለዚያም ፅናትሽን ስጭኝ ልጠጣው ኪዳነ ውሉን የኔ ፈቃድ እምነትሽ ነው ያንች ፍቃድ ብቻ ይሁን ።እንደ ጳውሎስ እንድፀና ፣በፍርሃት ሳልታሰር ለየዕለቱ ሞት እንዳልሰንፍ የኪዳኔ ቃል እንዳይነጥ ፍቃልሽ በሕሊናየ ዲብ ፣ ኃይልሽ በሕዋሴ ይረፍ ።ፍርሃት ቢያረብብኝም አንች ካለሽኝ አልሰጋም ኩርምት እችልበት ፣ እሸሸግበት አይጠፋም የግማደ መስቀሌን ጉጥ እታገስበት አላጣም አለዚያማ ብቻየን ነኝ ፣ ኢትዮጵያም ያላንች የላት አንች አፅኝኝ እንድፀናላት ።አስርጭብኝ የእምነት ቀንጃ ፤ለስጋቴ አጣማጅ አቻ ለጭንቀቴ መቀነቻ ።….አዎን ብቻየን ነኝ ፈራሁ እሸሸግበት ጥግ አጣሁ እምፀናበት ልብ አጣሁ …

ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ፲፱፻፷፩ ዓ.ም

One thought on “ትውስታ

Add yours

Leave a comment

A WordPress.com Website.

Up ↑